Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሶማሊላንድ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ያለመ ውይይት አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶማሊላንድ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር እና በቀጣናው ሰላም ማስፈንን ያለመ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በአሜሪካ የሶማሊያ አምባሳደር ሪቻርድ ሪሌይ እና የምስራቅ አፍሪካ የፀጥታ ግብረ ሀይል ኮማንደር ሜጀር ጄኔራል ብሪያን ቲ ካሽ ማን የተመራ የአሜሪካ ከፍተኛ ልዑክ ከተመራጩ የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ጋር በሀርጌሳ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ የአሜሪካ ልዑክ ሶማሊላንድ ያካሄደችውን ሰላማዊ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አድንቆ፣ አዲስ ለተመረጡት የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ሞሃመድ አብዱላሂ ኢሮ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግልፅ፣ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ ነበር ያለው ልዑኩ፤ ይህም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱን ገልጿል፡፡

በሶማሊላንድ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዕድሎችን በተመለከተ እንዲሁም በሶማሊላንድ እና አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙት ለማጠናከር ያለመ ምክክር አድርገዋል፡፡

አብዱራህማን ሞሃመድ አብዱላሂ ኢሮ÷ ከአሜሪካ ልዑክ ጋር ቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲን ለማስፋት ያለመ ምክክር ማድረጋቸውን በኤክስ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱ ሶማሊላንድና አሜሪካ ያላቸውን የጋራ ተልዕኮ የሚያረጋግጥ ነው ማለታቸውን ሆርን ዲፕሎማት ዘግቧል፡፡

Exit mobile version