አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከየደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ህዝቦች ድርጅት (ስዋፖ) ኔቱምቦ ናንዲ-ንዳይትዋህ ካለፈው ሣምንት አወዛጋቢ ምርጫ በኋላ የናሚቢያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን፥ ተመራጯ ፕሬዚዳንት ኔቱምቦ ናንዲ-ንዳይትዋህ ከ57 በመቶ በላይ ድምጽ ሲያገኙ፤ ተቀናቃኛቸው ፓንዱሌኒ ኢቱላ 26 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህም ኔቱምቦ ናንዲ-ንዳይትዋህ የመጀመሪያዋ የናሚቢያ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ተረጋግጧል።
ሆኖም የሎጂስቲክስ ችግርና በአንዳንድ አካባቢዎች ለሦስት ቀናት የሚቆይ የምርጫ ጊዜ መራዘሙን ተከትሎ ፓርቲያቸው የምርጫ ስህተት ተፈጽሟል ያለውን ውጤት እንደማይቀበሉ ተቀናቃኛቸው ገልጸው ነበር።
አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ ይፋ የሆነውን የውጤት መግለጫ ውድቅ ቢያደርጉም ተመራጯ ፕሬዚዳንት፥ ህዝቡ ለሰላምና መረጋጋት ድምጽ ሰጥቷል ብለዋል።
ሀገሪቱ ከፈረንጆቹ 1990 ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ የስዋፖ ፓርቲ ስልጣኑን እንደያዘ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡