የሀገር ውስጥ ዜና

ውጤት ማስመዝገብ የማይችሉ የትምህርት ቤት አመራሮች በአመራርነት መቀጠል እንደማይችሉ ተገለፀ

By Feven Bishaw

December 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥ ውጤት ማስመዝገብ የማይችሉ የትምህርት ቤት አመራሮች በአመራርነት መቀጠል እንደማይችሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ ፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ÷የትምህርት ስርዓቱን ካለበት ተግዳሮቶች ለማውጣት የችግሩን ምንጭ በጥናት መለየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ለስብራቱ ዋነኛው ክፍተት የትምህርት ቤት አመራሮች ሀላፊነታቸውን በተገቢው መልኩ መወጣት አለመቻል በመሆኑ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ መደረጉን አንስተው ይህንም ለመቅረፍ በተሻሉ አመራሮች የመተካት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል ፡፡

የትምህርት አመራሮች ውጤታማ ባለመሆናቸው ለቦታው የሚመጥኑ አመራሮችን በማወዳደር 2 ሺህ 783 የሚሆኑ አመራሮችን በማሰልጠን በየትህምርት ተቋማት መመደባቸውንም ገልፀዋል፡፡

ወደ ስራ የገቡት የትምህርት ቤት አመራሮች በሶስት አመታት ውስጥ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ለማድረግ ውል መግባታቸው የተመላከተ ሲሆን ÷አመራሩም በገቡት ውል መሠረት ሀላፊነታቸውን መወጣት ካልቻሉ ከአመራርነት እንዲነሱ ይደረጋል ብለዋል ።

በክልሉ ባለፈው አመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤት ተማሪው፣ መምህራንና መላው የትምህርቱ ማህበረሰብን ብርቱ ትጋት እንደሚሻ አመላካች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው