አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት (ዲያሌሲስ) አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ካሊድ ሸረፋ÷አገልግሎቱን ለማስጀመር ከማሽን ግዢ፣ ማሽን ተከላና የዘርፉን ሰብ-እስፔሻሊስት ሀኪም ማፈላለግ እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎችን ማሰልጠንን ጨምሮ ቅድመ ዝግጅቱ ጊዜ መውሰዱን አስታውሰዋል፡፡
የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በቀላሉ እንደማይገኝ በመግለጽ የአገልግሎቱ መጀመር የበርካቶችን እንግልት የሚቀንስና እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አገልግሎቱ በአግባቡ እንዲሰጥና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥም ተቋሙ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀው የክፍሉ ባለሙያዎች በትጋት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የስልጤ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
አገልግሎቱን በዘላቂነት ለማቅረብ የሕክምና ቁሳቁስ ስለሚያስፈልግ የህብረተሰቡ፣ የባለሀብቱ፣ የዳያስፖራው እና የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡