Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ – የተዛባ የዝናብ ሁኔታ፣ ከፍተኛ ሙቀትና ድርቅ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን ወደተለዋዋጭ የዝናብ ሁኔታዎች፣ ከፍተኛ ሙቀትና የድርቅ ጊዜያት እየከተታት መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ እየተካሄደ ነው፡፡

ጉባኤው በተለይ በረሃማነት ላይ ትኩረት አድርጎ “ዛሬ ምድራችንን ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት፤ በምድር ላይ ያለውን ብዝሃ ህይወት ዕጣ ፈንታ ይወስናል” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በምድር ላይ ያለውን ህይወት ለማስቀጠል እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት በረሃማነትን የመዋጋት ስምምነት (የዩኤንሲሲዲ) ዋና ፀሃፊ ኢብራሂም ቲያው፥ “ምድርን ዛሬ የምንከባከብበት መንገድ የወደፊት እጣ ፈንታዋን ይወስናል” ብለዋል።

ጉባኤው ከመላው ዓለም የተውጣጡ መሪዎችን፣ ባለሙያዎችንና የማህበረሰብ ተወካዮችን በማሰባሰብ የመሬትን መልሶ ማገገምና በረሃማነትን ለመዋጋት ያለመ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ኤጀንሲ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር እንዳለው የፈረንጆቹ 2023 ለዓለማችን ወንዞች በ30 ዓመታት ውስጥ ደረቃማ ዓመት ነበር፤ ሞቃታማው ዓመት የውሃ ፍሰት መድረቅን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች የተራዘመ ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡

በ2023 ዓለም እጅግ ሞቃታማው ዓመት የተባለ ሲሆን፥ ክረምትም እጅግ በጣም ሞቃታማ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ሞቃታማው ዓለም ወደተለዋዋጭ የዝናብ ሁኔታዎች፣ ከፍተኛ ሙቀትና የድርቅ ጊዜያት እየመራ እንደሆነ የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

Exit mobile version