አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወትን መለወጥ የሚችል የፈጠራ እምቅ አቅም እንዳለ በዓይናችን አይተናል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡባዊ ትብብር ድርጅት ጋር በመተባበር ከ14 ሀገራት የተወጣጡ 41 ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የሚቀርቡቡት ዓለም ዓቀፍ የቴክኖሎጂ አውደርእይ በሳይንስ ሙዝየም የመክፈቻ ፕሮግራም አካሂዷል።
ዓውደ-ርዕዩ ከተለያዩ አህጉራት ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ የጠበቀ ትብብር በመፍጠር እውቀትን በመጋራት የመፍጠርና የመጠቀም አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ የቴክኖሎጂ ዘርፍን ስኬታማ ለማድረግ በዘርፉ አቅም ከገነቡ ሀገራት ጋር በትብብር እየተሰራና ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ ዓውደ-ርዕዩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወትን መለወጥ የሚችል የፈጠራ እምቅ አቅም እንዳለ አይተናል ነው ያሉት፡፡
የደቡባዊ ትብብር ድርጅት ዋና ጸሃፊ መንሱር ቢን ሙሳላም÷ ዓውደ ርዕዩ ለስታርትአፕ፣ ለፈጠራ ባለሙያዎች እና በሀገሮች መካከል የተሻሉ የተግባር ልምድ ልውውጦችን እና የጋራ መማማርን በማበረታታት የቴክኖሎጂ ልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የስራ ፈጣሪዎችን እና ተማሪዎችን የቴክኖሎጂ አቅምን በማጎልብ የአባል ሀገራትን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለመፍጠር ያገለግላልም ማለታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አባል ሀገራት በሀገር በቀል ቴክኖሎጂው ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ የጋራ የሆነ አቅም ለመፍጠር ሰፋፊ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ትብብር ድርጅት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሃላፊ ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ናቸው፡፡