የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ አገኘች

By yeshambel Mihert

December 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደን አስተዳደር ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷን ይፋ አድርጓል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የደን አስተዳደር ስታንዳርድ የኢትዮጵያን የደን ልማት ዘርፍ በማጠናከር ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን ጥራትና ተፈላጊነት ያሳድጋል ተብሏል።

በተለይም የሥነ ምህዳር ተጽፅኖን ለመቀነስ እንደ ውሀ፣ ካርበን፣ ብዝሀ ህይወት እና መሰል ዘርፎችን ለመጠበቅ ያግዛል ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ እቅዷን እውን ለማድረግ በ2025 ዓ.ም 15 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬት በደን ለመሸፈን እየሰራች መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም÷የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ገልፀው የደን ልማት አስተዳደር ደረጃው የተጠናከረ የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የደን ጭፍጨፋን ማጥፋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ÷ የኢትዮጵያ የደን አስተዳደር ደረጃ መፅደቁ ኢትዮጵያና ምክር ቤቱ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ትብብር እና የጋራ ራዕይ የሚያንጸባርቅ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የደን አስተዳደር ምክር ቤት የደን ልማት አስተዳደርን በማሳደግ ምርታማና ምቹ ዓለምን ለመፍጠር በፈረንጆቹ 1993 የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።