Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብሪታኒያ በሳይበር ጥቃት 44 ቢሊየን ፓውንድ ማጣቷ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪታኒያ ባለፉት አምስት አመታት በተፈፀመባት የሳይበር ጥቃት 44 ቢሊየን ፓውንድ ማጣቷን ጥናቶች አመላከቱ፡፡

መቀመጫውን በለንደን ያደረገው እና ሎውደን የተባለው የኢንሹራንስ ቡድን ባወጣው ሪፖርት÷ ከፈረንጆቹ 2019 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ በብሪታኒያ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የግል ሴክተሮች የሳይበር ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡

የጥቃት ኢላማ የተደረጉት እነዚህ ሴክተሮች ከሀገሪቱ አጠቃላይ የቢዝነስ ተቋማቶች 52 በመቶውን ያህል የሚሸፍኑ ሲሆኑ በዓመት ከ100 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ገቢ ያላቸው መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ተቋማቱ የሳይበር ጥቃት የተፈፀመባቸው በተጠለፉ የኢ-ሜይሎች አድራሻዎች እና በመልዕክት ልውውጥ በተደረገ የመረጃ ምንተፋ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የብሪታኒያ መንግስት በሚቀጥሉት አምስት አመታት በመረጃ ደህንነት ላይ ትኩረት ማድረግ ከቻለ የጥቃቱን 70 በመቶ መከላከል ይችላል ያለው ቡድኑ÷ በዚህም ከ30 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ሊያድን እንደሚችል ጠቁሟል።

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪዎች እና መንግስት የሳይበር ደህንነትን በተመለከተ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝቧል።

በቅርቡ በተደረገ ጥናት በፈረንጆቹ 2023 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ8 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሳይበር ጥቃት መባከኑን ክሌም ጆርናል አስነብቧል።

Exit mobile version