አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፉ ላለፉት 80 ዓመታት ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ በአፍሪካ ጠንካራ አየር መንገድ መገንባት መቻሏ ተገለፀ።
የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሺን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በመተባበር በአፍሪካ ደረጃ ይከበራል።
ከበዓሉ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በጋራ በሰጡት መግለጫ÷ በዓሉ ‘አስተማማኝ ሰማይ ለዘላቂ ወደፊት’ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ እንደሚከበር ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የዓለም የሲቪል አቪዬሽን ሲመሰረት ጀምሮ ተሳትፎ በማድረግ በኢንዱስትሪው ቀዳሚ ሚናዋን ስትጫወት መምጣቷ እንዲሁም አሁን ላይ በአፍሪካ ቀዳሚና ጠንካራ አየር መንገድ መገንባት መቻሏም ተመላክቷል።
በፈረንጆቹ 1944 ታህሳስ ወር ውስጥ 52 ሀገራት በተሳተፉበት እና በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ በተካሄደው ጉባኤ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መመስረቱን መግለጫው አስታውሷል፡፡
ከአፍሪካ ከተሳተፉ ሶስት ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች እና ሲቪል አቪዬሽኑ በ2035 ዓ.ም በአፍሪካ ተመራጭና ግንባር ቀደም የአቪየሺን ማዕከል ለመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም በመግለጫው ተጠቅሷል።
አሁን ላይ አየር መንገዱ የበረራ መዳረሻዎቹን 141 ያደረሰ ሲሆን÷ በሀገሪቱ ያሉ ኤርፖርቶች ቁጥር 23 እንደደረሰና ከነዚህ ውስጥ አራቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ የያዙ ናቸው ተብሏል፡፡
የዓለምአቀፉ የሲቪል አቪዬሽን 80ኛ ዓመት ‘አስተማማኝ ሰማይ ለዘላቂ ወደፊት’ በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
በታሪኩ ለገሰ