Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ምህረት …

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጦር መሳሪያና ታክስ ተጠርጥሮ ሊቀጣ ለነበረው ልጃቸው ሀንተር ባይደን ምህረት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡

ሀንተር በዚህ ወር በፌደራል ወንጀል በጦር መሳሪያና ታክስ ማጭበርበር ክስ ቀርቦበት ለዓመታት ዘብጥያ ሊወርድ በተቃረበበት ወቅት አባቱ ምህረት እንዳደረጉለት ነው የተገለጸው፡፡

ለልጄ ሀንተር ምህረት እንደረግለት ፈርሜያለሁ፤ ስልጣን ከያዝኩበት ቀን ጀምሮ በፍትህ መምሪያው ውሳኔ ላይ ጣልቃ አልገባም ስል ቆይቻለሁ እናም ልጄ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሲከሰስ እያየሁም ቃሌን ጠብቄአለሁ ብለዋል፡፡

በልጃቸው ላይ የቀረበው ክስ ልክ እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ ምህረት እንዳደረጉለትም ተናግረዋል።

በልጃቸው ክስ በኮንግረስ ውስጥ ያሉ በርካታ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቼ እኔን ለማጥቃት ሆን ብለው የመዘዙት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሆኖም ይህ ተግባር የሀገሪቱን የፍትህ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ሲሉ የሚገልጹ አሉ፤ ከእነዚህም መካከል ተመራጩ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ይሄን ተከትሎ በሰጡት ሃሳብ ባይደን ለልጃቸው ያደረጉት ምህረት ፍትህን ማዛባት ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ልጃቸውን ኢቫንካን ያገቡ የጃሬድ ኩሽነር አባትና በታክስ ማጭበርበርና በሌሎች ክሶች ዘብጥያ እንዲወርዱ የተፈረደባችውን ቻርለስ ኩሽነርን ምህረት እንዳደረጉላቸው አስታውሶ የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

በአሜሪካ ፕሬዚዳንቱ ነጩ ቤተ መንግስትን ለተረኛ አስረክበው ከመውጣታቸው በፊት ምህረት ማድረግ የተለመደ ተግባር ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው ከ100 በላይ ለሆኑ ሰዎች ምህረት እንዳደረጉ ይነሳል፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ይቅርታ በፌዴራል ወንጀሎች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔዎችን እንደሚሰርዝ የሚገለጽ ሲሆን፥ በህግ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ይቆጠራል፤ ማንኛውንም ተጨማሪ ቅጣት እንዳይደረግ ያግዛል፤ እንደ ድምጽ መስጠት ወይም ለሹመት መወዳደር ያሉ መብቶችንም ይፈቅዳል።

Exit mobile version