ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአፍሪካ ፔንግዊን ዝርያ በ2036 ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንደሚችል ተመላከተ

By Mikias Ayele

December 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ፔንግዊን ዝርያ በፈረንጆቹ 2036 ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንደሚችል በርድ ላይፍ ሳውዝ አፍሪካ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ተወካይ ከርት ማርቲን ለስፑትኒክ እንደገለፁት÷ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ብርቅዬ የፔንግዊን ዝርያ ከባድ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል፡፡

በአህጉሪቱ ያሉ ጥንድ ፒንጉዊኖች ቁጥር ከ10 ሺህ በታች መሆኑን ጠቅሰው÷ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው የአፍሪካ ፔንግዊን ዝርያ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

የአፍሪከ ፔንግዊኖች የሚመገቡት ምግብ በቂ አለመሆን ለቁጥራቸው መቀነስ ምክንያ መሆኑን ጠቅሰው÷ ዝርያውን ከመጥፋት ለመታደግ ትብብር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ህብረት 18 የህልውና አደጋ ያጋጠማቸው ዝርያዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን የአፍሪካ ፔንግዊን ዝርያ የመጥፋት ስጋት አደጋ ከተደቀነባቸው መካከል በቀዳሚነት ስፍራ ተቀምጧል።

የአፍሪካ ፔንግዊን ዝርያ ባለፉት 100 ዓመታት 97 በመቶ መቀኑሱን ህብረቱ አስታውሷል።

በደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ በብዛት የተስፋፋው የአሳ ምርት ኢንዱስትሪ የአፍሪካ ፔንግዊኖች ቁጥር በፍጥነት እንዲቀነስ አንዱ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡