የሀገር ውስጥ ዜና

በታኅሣስ ወር ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል- ኢንስቲትዩቱ

By ዮሐንስ ደርበው

December 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥለው የታኅሣስ ወር ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ የታኅሣስ ወር የአየር ሁኔታን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስሩ ገጹ ባጋራው መረጃ÷ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አስገንዝቧል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ብሏል፡፡

እንዲሁም በምሥራቅ፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ጠቁሟል፡፡