የሀገር ውስጥ ዜና

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓና ፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

By Melaku Gedif

November 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓ እና ፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት ጋር ተወያዩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የተካሄደውን የሁለትዮሽ ውይይት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ግንኙነታቸውን ይበልጥ በሚያጠናክሩባቸው መስኮች ላይ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

በዋናነት በኢንቨስትመንት፣ በባህል፣ በቱሪዝም እንዲሁም በፀጥታና በመሠረተ ልማት ዙሪያ መምከራቸውን የገለጹት አምባሳደር ነቢያት፤ ባለፉት አመታት የሀገራቱ ግንኙነት እየጠነከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሚኒስትሮቹ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማትና በሀይል አቅርቦት ዙሪያ በትብብር መስራት ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከራቸውንም ጠቁመዋል።

ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር ናት ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይህንንም ለማሳደግ በርካታ ስራ በትብብር እንደሚሰሩ ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

ፈረንሳይ በባህልና ቅርስ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ትብብርና እገዛ ማድረጓ የተነሳ ሲሆን፤ ለአብነትም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የኢዮቤልዩ ቤተመንግስት እድሳት ላይ ፈረንሳይ መሳተፏ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረጓ የፈረንሳይ ባለሀብቶች መጥተው እንዲያለሙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬ