Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያከናውኑ የነበረውን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲያከናውኑ የነበረውን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በሰነድ መልክ የተዘጋጀውን የፖለቲካ ፓርቲዎቹን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ተረክበዋል።

ሰነዱ በኢትዮጵያ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከታሕሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲደረግ የቆየ የውይይት ቃለ ጉባዔ ሰነድ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ላለፉት ዓመታት የተካሄደው ውይይት በ8 ዋና ዋና አጀንዳዎችና በ50 ንዑስ አጀንዳዎች ዙሪያ መካሄዱም ተገልጿል።

ሰነዱ ለሀገራዊ ምክክር ሥራዎች በግብዓትነት የሚያገለግል ይሆናል መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ውይይት ለሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ዕድገት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው።

ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትም ትልቅ ፋይዳ ያለው ውይይት መሆኑን አንስተው፤ ፓርቲዎች ተቀራርበው ከመከሩ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት ይቻላልም ነው ያሉት።

የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉም ከውይይቱ መረዳት መቻሉን ጠቁመው፤ የመደማመጥ ባህልን ያሳደግ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች ልዩነቶችን በማክበር በመተባበርና በመደማመጥ ውይይቱን ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውይይቱ ትልቅ ልምድ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ ለዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታም የራሱ ትልቅ ሚና የሚጫወት ውይይት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

Exit mobile version