አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ እና ከኤክስፐርታይዝ ፍራንስ ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ተፈራርማለች፡፡
ስምምነቱ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲሰማሩ ለማድረግ እና ሰብዓዊ ልማትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰመሪታ ሰዋሰው÷ ኢትዮጵያ የፈረንሳይ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደምታደንቅ ገልፀው ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክር ገልፀዋል፡፡
የኤክስፐርታይዝ ፍራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀርሚ ፔሌት÷ድርጅታቸው በመንግስት ኢንተርፕራይዞች፣በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ የአጋርነት ትብብር እንዲሁም በሀገር በቀል ኢኮኖሚውን ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ድርጀቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን ማጠናከርን ጨምሮ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ላሉ ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን የድጋፍ መጠን ከፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመደግፍ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችል የኤክስፕርታይዝ ፍራንስ ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ እንደሚቋቋምም ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ጠቅሰው ኤክስፐርታይዝ ፍራንስ በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡