አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ በዓላት እሴቶችን በማስተዋወቅ ለሕዝቦች አብሮነት እና ዘላቂ ሠላም ግንባታ መጠቀም ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
የኣሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ “ዲሽታ-ግና” በዓል በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል፡፡
ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ህዝባዊ በዓላት ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የሕግ እና አስራር ሥርዓት በመዘርጋት ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ህዝባዊ በዓላት ሲክበሩ የህዝቦችን የእርስ በርስ መልካም ግንኙነት እና ትስስር በሚያጎለብትሁኔታ እንዲከበር የተለያዩ ስራዎችን እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የኣሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ የሆነውና ከብሄረሰቡ ጋር አብሮ የኖረው ድሽታ-ግና በዓል በውስጡ በርካታ ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችን የያዘ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ቂምና ቁርሾ እንዲጠፋና ሰላም እንዲወርድ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ አብሮነትን ማጠናከር፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ፈጣሪን ማመስገንና ቤትና አካባቢን ማጽዳት የበዓሉ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው÷ የመከባበር፣ የመረዳዳት፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የፍቅር ፣ የምስጋናና የአካባቢ ፅዳት የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ድሽታ-ግና በዓል መገለጫዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ድንቅ ባህል በመጠቀም በአካባቢው ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት በዚህ ባህላዊ ዕሴት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
ከከፋፋይ ትርክት ይልቅ የወል ትርክትን እና የሀገር ግንባታን እውን ለማድረግ የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የፍቅር መገለጫ የሆኑ ባህሎቻችንን አጉልተን መጠቀም አለብን ሲሉም አጽንኦት መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡