አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሰለጠናቸውን የተለያዩ ሙያተኞች አስመርቋል።
አየር ኃይሉ “የተከበረች ሀገር የማይደፈር አየር ሀይል” በሚል መሪ ሀሳብ 89ኛ የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ አብራሪዎች፣ እጩ መኮንኖች፣ መደበኛ ቴክኒሺያኖች፣ ደረጃ 7 ቴክኒሻኖች፣ መሰረታዊ ወታደሮችን እና ፈልጎ ማዳን ኮማንዶ ሰልጣኞችን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፤ አየር ኃይሉ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ስኬቶች አስመዝግቧል።
ጠንካራ አየር ኃይል ለመገንባት የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሰው ሃይል ግንባታ እና ትጥቆችን የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው በማለት ገልጸው፤ ከሌሎች ሀገራት ዕውቀትና ልምድ የሚገኝበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ በአነስተኛ ኪሳራ ለማሸነፍ የውጊያ ዝግጁነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
አየር ኃይሉን ብቁና ጠንካራ ለማድረግ ውጤታማ ስራዎችን እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሰራዊቱን የስነ ልቦና ግንባታን ጨምሮ የወታደራዊ ትጥቆች አቅም የማሳደግ መሰራቱን አመላክተዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጅን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ የአየር ሃይል የሠራዊት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በታሪኩ ለገሰ