የሀገር ውስጥ ዜና

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የቻይና ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አሥተዳደር በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

By ዮሐንስ ደርበው

November 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የቻይና ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አሥተዳደር በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ የቻይና ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አሥተዳደር የውጭ ዜጎች አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ቼን ዮንግሊ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም አገልግሎቱ ሪፎርም ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ጎሳ÷ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ዜጎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች የሚገቡ የቻይና ዜጎች የኢትዮጵያን ሕግ እና ሥርዓት ተከትለው እስከሠሩ ድረስ ተቋሙ እገዛ ያደርጋል ማለታቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

አገልግሎቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በተሻለ መልኩ እንዲያከናውን የቻይና መንግሥትና የቻይና ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አሥተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና በጋራ መሥራት እንደሚችሉም አረጋግጠዋል።

የተቋማቱን ትብብር በሕግና አሠራር ማቀናጀት ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ጠቃሚ መሆኑም ተነስቷል፡፡