የሀገር ውስጥ ዜና

ፓርቲያችን ብልፅግና በሪፎርም የተመዘገቡ ድሎችን ወደ እመርታ ለማሸጋገር እየተዘጋጀ ነው – አቶ አደም ፋራህ

By ዮሐንስ ደርበው

November 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓርቲያችን ብልፅግና በሪፎርም የተመዘገቡ ድሎችን ወደ እመርታ ለማሸጋገር እየተዘጋጀ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

“የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል የሚከበረውን የፓርቲውን 5ኛ ዓመት አስመልክቶ በማህበራዊ ርስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ አደም ፋራህ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

“ፓርቲያችን ብልፅግና ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም በለውጥ ትግል ውስጥ ተወልዶ በአዲስ እይታ፣ አዲስ ምዕራፍ ከፍቶ እያደገ ያለ፣ ባለፉት 5 ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻለ እና ዛሬ ላይ ደርሶ በሪፎርም የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠልና ወደ እመርታ ለማሸጋገር በብቃት እየተዘጋጀ ያለ ፓርቲ ነው።

ትናንት በሕዝባችን የለውጥ ፍላጎት እና ተራማጅ የለውጥ እሳቤን ባነገቡ ብርቱ መሪዎቻችን ጥረት ታግዘን የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ብልፅግና ፓርቲን ወልዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን የአለም ፈርጥ ምድራዊት ኮኮብ ሊያደርጉ የሚችሉ መሰረቶችን ጥሏል።

በልዕልና መር የህልም ጉዟችን ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ለነገ የቤት ስራችን አቅም ሆነው ለተጨማሪ ድሎች እና ስኬቶች እንድንተጋ የሚያደርጉ ወረቶቻችን ሆነው ዛሬ ላይ ደርሰናል።

ያልታዩ እምቅ ሀብቶችን ፈልፍለን አውጥተን፣ በአቧራ የተሸፈኑ እልፍ ውበቶችን ገልጠን፣ አይደፈሬ የሚመስሉ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠን፣ ሀገርን ከብተና አድነን፣ በሁላችን ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ህብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሌት ተቀን ለፍተናል።

እያንዳንዱ ሰኮንድ እና ደቂቃ ያለ ትጋት እንዳያልፍ በመደመር ሳንካዎች ማለትም በዋልታ ረገጥነት፣ በጊዜ ታካኪነት፣ በአቅላይነት፣ ሙያን በመናቅና በፌዘኝነት የሚባክን ጊዜ እንዳይኖር በፍጥነትና ፈጠራ የገሰገስንበት መንገድ የፓርቲያችንን 5ኛ አመት የምስረታ በዓልን በሁለንተናዊ ድሎች ታጅበን የምናከብርበት ጊዜ ላይ ሊያደርሰን ችሏል።

የለውጡን ጉዞ ስንጀምር ተስፋ የሰጠነው ሕዝባችን በእኛ ላይ ያለውን እምነት አሳይቶ በካርዱ መርጦ ለኃላፊነት ሲያበቃን የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግሮች ፊት ለፊት ተጋፍጦ ለማሸነፍ ሀገር በቀል እሳቤዎች፣ አቅሞችና የሕዝባችን ያልተቆጠበ ድጋፍ ስንቅ ሆነውን በሰራናቸው ስራዎች በእርግጥም ስርዓት ለመገንባት እና የሕዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል ያስቻሉን ስኬቶችን አስመዝግበናል።

ስለ ልማት ስናወራ ግንባር ቀደም ምስክር ሆነው የሚቀርቡት ሀሳቡን፣ ገንዘቡን እና ቴክኒካል አቅሙን ከየት አመጣችሁ ብለው ብዙ የውጭ እንግዶች የሚጠይቋቸው በየቀኑ ያስመረቅናቸው የአሻራ ፕሮጀክቶች፣ በገጠር በከተማው በፍትሀዊነት መርህ ያዳረስናቸው ትሩፋቶች፣ ካዘመሙበት የተቃኑ የደሀ ጎጆዎች እንጂ ያልተጨበጡ ተስፋዎችና ያልተዳሰሱ እምርታዎች አይደሉም።

ስንዴን የሀገር ወስጥ ፍላጎታችንን ከማሟላት አልፈን ኤክስፖርት ያደረግነው፣ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ነፍስ የዘራንበት፣ የዲፕሎማሲ መልህቃችን ከብሪክስ + ጥምረት ጋር የቀላቀለን፣ ተቆጥረው የማያልቁ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ያስመዘገብነው በሕዝባችን ሁለንተናዊ ድጋፍ ታጅበን መሆኑን ፈፅሞ አንረሳም። ልባዊ ምስጋናችንም እናቀርባለን።

በሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የተወረወሩብንን የጥፋት ቀስቶች የመከኑት ችግሮችን በብልሀት የመፍታት ጥበብን በማዳበራችን፣ በፈተናዎች የማይዝል የደነደነ ትከሻን በመጎናፀፋችን፣ ለልማት እና ለብልፅግና የቀደመ ብሩህ እሳቤ በመከተላችን፣ ከምንም በላይም ከፈጣሪ ድጋፍ ማግኘታችን ጭምር ነው።

“የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየውን የፓርቲያችን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ሀገራዊ ማጠቃለያ መርሃ ግብር በነገው እለት ለማካሄድ የተዘጋጀን ሲሆን በአጠቃላይ በዓሉ ለተጨማሪ ድሎች ኃይላችንን የምናድስበት፣ ለሃሳብ ልዕልና እና በሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ያለንን ቁርጠኝነት የምናረጋግጥበት እንደሚሆን እምነቴ ነው።

“የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና”