Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሲዳማ ክልል የግርብና ስራን ለማዘመን የተለያዩ ኤኒሼቲቮች እየተተገበሩ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ አውደ ጥናት በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ እንዳሉት÷ የክልሉን ኑሮ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የላቀ ጥረት በማድረግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ዜጎች በፍኖተ ካርታው የመንግስትን ዓላማ በአግባቡ ተገንዝበው በልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን በቁርጠኛ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው ያሉ አቅሞችና ዕድሎችን በመለየት እንዲሁም ተግዳሮቶችን በማመላከት የግብርና ስራን ለማዘመን ሚናው ጉልህ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት የታየውን ተሞክሮ በፍኖተ ካርታው ውስጥ በማካተት ለአመርቂ ውጤት በትኩረት መስራት እንደሚገባ መጠቆማቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ፍኖተ-ካርታውን በብቃት መተግበር ያለውን ጠቀሜታ ገልጸው ለተግባራዊነቱ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ማዕከላት፣ ከግሉ ሴክተር እና ከልማት አጋሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል።

የፍኖተ-ካርታው ባለቤትነት በክልሉ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የተለያዩ ሴክተሮች መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

Exit mobile version