የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ ኤግዚብሽንና ሲምፖዚዬም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ዓቅም ያንጸባረቁ ናቸው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

By Feven Bishaw

November 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ ኤግዚብሽንና ሲምፖዚዬም እንዲሁም የአፍሪካ መሠረተ ልማት ፕሮግራም ሳምንት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ዓቅም በተጨባጭ ያንጸባረቁ ናቸው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለፁ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ ላለፉት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄዱ የቆዩት የኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ ኤግዚብሽን እና ሲምፖዚዬም እንዲሁም የአፍሪካ መሠረተ ልማት ፕሮግራም ሳምንት በስኬት መጠናቀቃቸው የሚያኮራ ነው ብለዋል።

እነዚህ ሁነቶች የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ዓቅም ብሎም የአረንጓዴ ልማት ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያንጸባረቁ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ሁለንተናዊ የመሠረ ልማት ዕድገት፣ በታዳሽ ኢነርጂና ትስስር ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ማዕከላዊ ሚና በሁነቶቹ አማካኝነት ማሳየት መቻሉንም በፅሁፋቸው አስፍረዋል።