Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላትጋር መግባባት እየተፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር እየተደረገ ባለው ውይይት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።

የክልሉ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ለኦሮሞ ሕዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ ሲባል ልዩነትን ለማጥበብና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብሏል።

በውይይቱም በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑንም መግለጫው አረጋግጧል።

ለውጡ ከመጣ ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ለተለያየ ችግር የሚጋለጠው የውስጥ አንድነት በማጣቱ መሆኑ ታምኖበት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህዝቡ አንድነት ያልተነሳበት መድረክ እንዳልነበረ በመግለጫው ተመልክቷል።

ሲደረግ የነበረው የሰላም ጥሪም ያለማቋረጥ እንደነበረ ገልጾ የኦሮሞ ህዝብ በተለያየ ጊዜ ያደረጋቸው ትግሎች ፍሬ ያላፈሩት በውስጥ አንድነት እጦት መሆኑን መግለጫው አክሎ አትቷል።

የለውጡ መምጣትም የኦሮሞን ህዝብ አንድነት የበለጠ እንደሚያጠናክር በማመን የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተሰራው ስራ ትልቅ እድል እንደነበረ ተመልክቷል።

በወቅቱ መልካም ጅማሮዎች እንደነበሩ ቢታወቅም ብዙም ሳይቆይ በመሳሳብና አንዱ ለሌላው እንቅፋት በመሆኑ ችግሩ ለስድስት ዓመታት እንደዘለቀም ተጠቅሷል፡፡

ህዝቡም ያልተገባ መሰዋእትነት እንዲከፍል መገደዱን ያተተው መግለጫው የስድስት ዓመታቱ የለውጥ ጉዞ በሰላማዊ ጉዞ የታጀበ ቢሆን ሮኖ ብዙ ርቀት መጓዝ ይቻል እንደነበረም አንስቷል።

ችግሩ እንዲቆምና በኦሮሞ መካከል አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ እንደ መንግስትም ሆነ እንደ ብልጽግና ፓርቲ የሰላም ጥሪ ያልቀረበበት ጊዜ እንደሌለም መግለጫው አስታውሷል።

ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር የተደረገው የሰላም ውይይት ባይሳካም ተስፋ በመቁረጥ የሰላም መንገዱ እንዳልተዘጋና ይልቁንም በተከታታይ የሰላም ጥሪ ሲቀርብ እንደነበረ መግለጫው ጠቁሟል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብም እንደ ባህሉና እንደ ወጉ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን እነዚህ የሰላም ጥሪዎች ውጤት አላፈሩም ማለት አይቻልም ሲል መግለጫው አንስቷል።

በሺህ የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ተመልሰዋል፤ የተሃድሶ ስልጠና ወስደውም ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ለብዙዎቹም የስራ እድል ተፈጥሯል ብሏል።

ሰሞኑን በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም በርካታ ወጣቶች የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆኑን ያብራራው መግላጫው ሰላምን ተጠምቶ የነበረው ህዝብም የክብር አቀባበል እያደረገ እንደሚገኝ አንስቷል።

አሁንም ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የሚቻለው ከቡድኑ አመራር አባላት ጋር ስምምነትና መግባባት ሲፈጠር በመሆኑ ከቡድኑ አመራሮች ጋር ያልተቋረጠ ውይይት ሲደረግ መቆየቱም በመግለጫው መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል።

ውይይቱም በክልሉ ውስጥ እርቅና ሰላም ማውረድ ላይ አተኩሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የሰላም መንገድ አዋጭ መሆኑን ከተቀበሉ አመራርና አባላት ጋር በተደረገው ውይይት መግባባት እየተፈጠረ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና ለሰላም የተከፈተው በርም ክፍት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

Exit mobile version