የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ”ጸሐይ 2” የተሰኘች አውሮፕላን ለበረራ ብቁ ማድረጉን አስታወቁ

By Amare Asrat

November 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ያከናወነው የሪፎርም ስራ ኢትዮጵያን የሚመጥን እና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት ጠንካራ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

አየር ኃይሉ 89ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ባለበት በዚህ ወቅት ”ጸሐይ 2” የተሰኘችና በአየር ኃይሉ የተሰራች አውሮፕላን ለበረራ ብቁ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

አውሮፕላኗ ግዳጅን በብቃት መፈጸም የሚያስችል ቴክኖሎጂ የታጠቀች ናት ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ይህም አየር ኃይሉ በ2030 በአፍሪካ ስመጥር አየር ኃይል ለመሆን የያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡