የሀገር ውስጥ ዜና

የኬንያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የመከላከያ ተቋማትን ጎበኙ

By Melaku Gedif

November 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሃሪሪ የመከላከያ ሰራዊት ተቋማትን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም የመከላከያ ዩኒቨርሲቲን፣ጋፋት አርማመንት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪን ፣ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪን እና የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሁለቱ እህትማማች ሀገራት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በወታደራዊ ዲፕሎማሲ መስክ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ሁለቱ ሀገራት ረጅም ድንበር እንደሚጋሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ÷ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ሽብርተኝነትን በመከላከል በኩል በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጉብኝት ያደረጉባቸው የመከላከያ ኢንዱስትሪ ተቋማት የሚሰሯቸው ስራዎችም የሚደነቁ ስለመሆናቸው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጥሩ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ እንደተገነዘቡ መግለጻቸውንም የከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡