ቴክ

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የኑክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆኗን ገለጹ

By yeshambel Mihert

November 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማጠናከርና ራሱን የቻለ የኑክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆኗን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኦስትሪያ ቬና እየተካሄደ ባለው የቴክኒክ ትብብር ፕሮግራም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሚኒስትሩ፤ በኒውክሌር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና አፕሊኬሽን ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረቻቸውን ስራዎችና ትብብሮች በተመለከተ ንግግር አድርገዋል።

የኒውክሌር ሳይንስ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማረጋገጥ አንገብጋቢ የሆኑ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን በመወጣት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ይህንን የተረዳ እቅድ በመያዝ በመስራት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር፣ የኒውክሌር ህክምናን ለማስፋፋት እና ራሱን የቻለ የኑክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ መስራች አባል ለሆችው ኢትዮጵያ ከኤጀንሲው ለሚደረግላት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የድርጅቱ ተባባሪ አካላትና አባል ሀገራት አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ እንዲያጠናክሩም መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡