አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ ነፃነት ወርቅነህ (ፕ/ር) ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የወባ በሽታ ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወባ በሽታ አሁን ላይ በክልሉ 18 ዞኖችና 10 ከተሞች ውስጥ መከሰቱን ጠቁመው÷ 39 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ለበሽታው ስርጭት ተጋላጭ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ወደ ጤና ተቋማት መጥተው ምርመራ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ቢሮው በክልሉ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል ግንዛቤ የማስጨበትስራን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በደሳለኝ አበራ