Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የገንዘብ ሚኒስቴር እና የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደረሱ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር እና የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

የገንዘብ ማኒስትሩ አህመድ ሺዴ ከባንኩ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኩውን ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው የትብብር መስኮች ላይ መክረዋል።

እንደ ሀገር እየተሰራበት ባለው የረጅም ጊዜ የእድገት ፕሮግራም፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ሌሎችንም ተግባራት ኢትዮጵያ እያከናወነች መሆኑን ለባንኩ አመራሮች አስረድተናል ሲሉ አቶ አህመድ ተናግረዋል።

ባንኩ መሠረተ ልማት ላይ ፋይናንስ የሚያደርግ ግዙፍ ዓለም ዓቀፍ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሳተፍ ተወያይተናል ብለዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ለምትገነባው አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ሆነው ፋይናንስ እንዲያደርጉ ተወያይተናል በማለት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ላይ እያደረገች ባለው የልማት እንቅስቃሴ ላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ መግባባታቸውንም ጠቁመዋል።

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩውን በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የተለያዩ የልማት ስራዎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚሁ ውጤታማነትም ከሌሎች አጋር የፋይናንስ ተቋማት ጋር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

Exit mobile version