አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመንደር አጀንዳ ተላቅቀን በዓለም መድረክ የሚገባንን የመሪነት ሚና መጫወት አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የፎቶ አውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዝዬም ተከፍቷል፡፡
አውደ ርዕዩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የከፈቱ ሲሆን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የፓርቲው አመራሮች እና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ብልጽግና አካታችነትን ለመተግበር አዳዲስ አካሄዶችን ተጠቅሟል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀዳሚው ግንብ ማፍረስ በሚል ዳርና መሐል፣ ዋናና – አጋር፣ ዳያስፖራና ሀገር ቤት፤ ሕዝባዊ መሠረትና – ሕዝባዊ መሠረት ያልሆነ፤ የሚሉ ሕዝብን የሚለያዩ ግንቦችን አፍርሷል እያፈረሰም ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ራሱም የለውጡ መሪ ሆኖ አንድ ኅብረ ብሔራዊነት ያለው እና በሐሳብ ላይ የተመሠረተ ፓርቲ መገንባቱንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ አያሌ ታሪካዊ ስብራቶች የገጠሟት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ስብራቶቹ በየጊዜው እየተናጉ ዕድገቷን ይጎትታሉ፤ ሕዝቦቿን ያጋጫሉ፤ ለጠላት በር ይከፍታሉ እንዲሁም ጥንካሬዋን ያዳክማሉ ሲሉም ገልጸዋል።
ስብራቶችን ለመጠገን እንደ ሀገር ለዘመናት ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት እንዲቻል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል በማለት ጠቅሰው፤ ለዘመናት የቆዩ የፖለቲካ ቁስል ለማከም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ዘርግተናል፤ ከትጥቅ ጋር የነበረንን ፖለቲካዊ ጋብቻ ለማፍረስም የተሐድሶ ኮሚሽን ተመስርቷል ብለዋል።
በተጨማሪም አያሌ መሥዋዕትነት ሲያስከፍሉ የቆዩ ነጠላ ትርክቶችን በመቀየር አሰባሳቢ ወደ ሆነው ገዥ ትርክት ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመንደር አጀንዳ ተላቅቀን በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ኢትዮጵያ የሚገባትን የመሪነት ሚና መጫወት ይኖርባታል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የጸጥታ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አንስተው፤ ከዚህ በኋላ ድህነትን ለማሸነፍ የሚውሉ የምርት መሣሪያዎች እንጂ ለእርስ በርስ ግጭት ማባባሻነት የሚውሉ ጠመንጃዎች በትከሻችን ላይ ቦታ ሊያገኙ አይገባም ነው ያሉት።
ይህ ጥሩ ያልሆነ የፖለቲካ ባህል ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ አይገባም ለዚህም እንደ ፓርቲ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ያለ እረፍት ይሰራሉ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፡፡
በፍሬህይወት ሰፊው