Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአቴከር ሕዝቦች የባህል ፌስቲቫል በኡጋንዳ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በባህል የሚያስተሳስረው የአቴከር ሕዝቦች የባህል ፌስቲቫል በኡጋንዳ በድምቀት ተከፍቷል።

“የጋራ ቅርሶችን በማክበር፣ ወደ ሰላም፣ ብልጽግና እና የባህል ህዳሴ ጎዳና ማምራት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው ፌስቲቫል መክፈቻ ላይ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጀሲካ አሉፖ ታድመዋል።

በፌስቲቫሉ ኢትጵያን በመወክል የአቴከር ሕዝቦች የበላይ ጠባቂ የሆኑት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገብረ መስቀል ጫላና የባህልና ስፖርት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

በተጨማሪም በፌስቲቫሉ የኬኒያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የደቡብ ሱዳን የጤና ሚኒስትር፣ የቱርክ፣ የቻይና፣ የሩሲያ፣ የታንዛኒያ እና የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በተገኙበት የመክፈቻ ፕሮግራሙ ተካሂዷል።

በፌስቲቫሉ የተካተቱ አቴከር ተናጋሪ የሆኑት ከኢትዮጵያ ኛንጋቶም፣ ቶፖታ እና ባሪ፣ ከደቡብ ሱዳን ቶሪት፣ ኢቴሶ፣ ቱርካና እና ማሳይ፣ ከኬኒያ ኢቴሶ፣ ካሪሞጆንግ፣ ጂዬ፣ ዶዶት፣ ኩማም፣ ላንጊ እና ካክዋ ማህበረሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በተመሳሳይ ከኡጋንዳና ከታንዛኒያም ቁጥራቸው የበዛ ማሳይ እና ሌሎችም በምስራቅ አፍሪካ በባህልና ቋንቋ የተሳሰሩ ማኅበረሰቦች በፌስቲቫሉ መሳተፋቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version