የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ጣልያን በሴቶችና ሕጻናት ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

By Feven Bishaw

November 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በጣልያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴዔታ ጆርጂዮ ሲሊ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጣልያንና ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው ÷ጣልያን የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋርና በልማት ትብብርና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የምታደርገውን ጠንካራ ተሳትፎ አድንቀዋል።

ጣልያን በቀጣይ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶችን እንድትደግፍ ጠይቀዋል ።

ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለማስፋት በጋራ መስራት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ጆርጂዮ ሲሊ በበኩላቸው÷ ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር የሁለትዮሽ ስምምነትን ለመፈረም ጣልያን ዝግጁ እንደሆነች መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡