የሀገር ውስጥ ዜና

አገልግሎቱ የኦዲት ግኝቶችን በማስተካከልና አሰራሩን በማሻሻል ሪፖርት እንዲያቀርብ ተጠየቀ

By Melaku Gedif

November 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የፋይናንስና ሌሎች የአሠራር ጉድለቶቹን እንዲያርምና የሕዝብ ቅሬታና እሮሮ የሚቀርብባቸው አሠራሮቹን እንዲያሻሽል ተጠየቀ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2015/16 ኦዲት ዓመት በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስና ሌሎች አሠራሮች ላይ የሂሳብ እና የክዋኔ ኦዲት አድርጓል፡፡

ይህን ተከትሎም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሁለት ክፍለ ጊዜ ተከፍሎ በሒሳብና በክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት በተቋሙ የሂሳብ አሠራር ላይ ከተገቢ የሂሳብ አርዕስት ውጪ የተመዘገበ 11 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ በኦዲት መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም 89 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ መመሪያን ያልተከተለና ያለውድድር ቀጥታ ግዥ እንዲሁም ከኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ስርዓት ውጪ በመደበኛ አሠራር የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ግዥ መፈጸሙ ተጠቅሷል፡፡

5 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ፣ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ተከፋይ ሂሳብ እንዲሁም 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በስራ ላይ አለመዋሉን ጨምሮ ሌሎች የሒሳብ አሠራር ክፍተቶች መታየታቸው ተገልጿል፡፡

በግኝቶቹ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች÷ የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ እንደሆኑ ማረጋገጣቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መረጃ ያመላክታል፡፡

በኦዲቱ የታዩ ግኝቶችን ጨምሮ ቀደም ሲል የነበረውን ብልሹ አሠራር ለመቅረፍ የሚያስችል ባለ 11 አጀንዳ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው÷ ጥረት እየተደረገበት ያለው የኢ-ፓስፖርት ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ ሲተገበር ችግሮቹ እንደሚፈቱ አብራርተዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው÷ አገልግሎቱ ተቀባይነት በሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ውስጥ የሚገኝ እንዲሁም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚማረሩበትና ቅሬታ የሚቀርብበት ተቋም መሆኑን አንስተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ÷ የተቋሙ የስራ ባህሪ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጥ በመሆኑ የተጀመረው የሪፎርም ስራ መጠናከር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሕግን ያልተከተለ የገቢ አሰባሰብ፣ ከመመሪያ ውጪ የሆነና በሚመለከተው ህጋዊ አካል ሳይፈቀድ የሚከፈል የትርፍ ሰዓት ክፍያ ህገወጥ አሠራር መሆኑን ገልጸው÷ የኢ-ፓስፖርት አሠራርን በማጠናከር ለሁሉም ተገልጋይ እኩል የሆነ መስፈርትንና ህግን የተከተለ የፓስፖርት አሠጣጥን በመተግበር ይገባል ብለዋል፡፡

የጎደለው የመንግስት ጥሬ ገንዘብ እንዲመለስ አሳስበው፤ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች የሚመዘገቡት በቅድሚያ ከማን እንደሚሰበሰቡና ለማን እንደሚከፈሉ ሲታወቅ በመሆኑ ይህንን የሚገልጹ ሰነዶች መቅረብ አለባቸው ብለዋል፡፡

ለሶስተኛ ወገን የሚተላለፉ የአገልግሎት ግዢዎች አዋጭነታቸው ተጠንቶና የግዥ መመሪያን ተከትለው መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ÷ በአገልግሎቱ ላይ የታዩ የሂሳብም ሆነ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ተቋማዊ መሠረታዊ የአሠራር ክፍተቶችን ያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ያልተስተካከሉ አሠራሮችን በማረም፣ ተገቢ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድና የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በማጠናከር ተቋሙ አሰራሩን አሻሽሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፈጻጸም ሪፖርቱን እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡