አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከደረሱት ሰብሎች 53 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቦ ወደ ጎተራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ እንዳሉት÷ በዘንድሮ የመኸር ወቅት 607 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
የታቀደውን ግብ ለማሳካትም የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር የደረሱ ሰብሎችን በጥንቃቄ ሰብስቦ ወደ ጎተራ ማስገባት ይገባል ብለዋል፡፡
እህሉን በወቅቱ ከማሳ አለመሰብሰብ፣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን አለመጠቀም፣ በወቅቱ ወቅቶ ወደ ጐተራ አለማስገባትና እህሉ ተገቢውን የእርጥበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ወደ ጎተራ ማስገባት የድህረ-ምርት ብክነትን የሚያስከትሉ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የጎተራ ተባዮችን ሊቀንስ የሚችል የእህል ማከማቻ አለመጠቀም፣ የከረመና አዲስ እህልን ቀላቅሎ ማስቀመጥ፣ የጎተራና እህል ማከማቻዎችን በአግባቡ ያለማፅዳት እና ፀረ- ተባይ መድሃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀም በዋነኛነት የድህረ-ምርት ብክነትን እንደሚያስከትሉ ጠቅሰዋል፡፡
በብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ መሰረት በሚቀጥሉት ቀናት ከሚኖረው የአየር እርጥበት ጋር ተያይዞ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል አቶ ኢሳያስ ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም የደረሱ ሰብሎችን በጊዜ በመሰብሰብ በጥንቃቄ ወደ ጎተራ ማስገባት እንዳለበት ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡