አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የአሜሪካ ዶላር ግዢ ከዛሬ ጀምሮ ማቆሙን አስታወቀ፡፡
የሩሲያ ባንክ እንዳስታወቀው፥ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በሀገር ውስጥ ምንዛሪ ላይ የሚደረጉ የውጭ ምንዛሪ ግዢዎችን የገበያውን ተለዋዋጭነት ለመቀነስ የዶላር ግዢው ተቋርጧል።
ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የሩሲያ ምንዛሪ የመግዛት አቅም መዳከሙን ተከትሎ እንደሆነ ገልጾ፥ በትናትናው ዕለት አንድ የአሜሪካ ዶላር 114 ሩብል ይሸጥ እንደነበር ጠቅሷል።
ሆኖም የውጭ ምንዛሪ መሸጡን እንደሚቀጥል የገለጸው ባንኩ፤ የውጭ ምንዛሪ ግዢ መቼ እንደሚቀጥል የሚወሰነው ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡
የሩብል የመግዛት አቅም መዳከምን ለማስቆም የዶላር ግዢን የማቋረጥ ተመሳሳይ እርምጃ ባለፈው ዓመት መውሰዱን አርቲ ነው በዘገባው ያስታወሰው።
የሩብል የመግዛት አቅም እየተዳከመ የመጣው የምዕራባውያን ማዕቀቦችና እየተባባሰ የመጣው የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶችን ተከትሎ እንደሆነም ይነገራል።
አሜሪካ ባለፈው ሣምንት በሩሲያ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ገደቦችን አክላለች፤ ይህም የሀገሪቱን ሦስተኛ ትልቁን ባንክ ጋዝፕሮም ባንክን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ዘገባው ገልጿል።