የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች በተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ላይ ተስማሙ

By ዮሐንስ ደርበው

November 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የተራዘመ የብድር አቅርቦት ማዕቀፍ (ኤክስቴንድድ ክሬዲት ፋሲሊቲ) ሁለተኛ ግምገማ ላይ በባለሙያዎች ደረጃ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ግምገማ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ 251 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚለቀቅ ተገልጿል።

የተራዘመ የብድር አቅርቦቱ ለአራት ዓመት የሚቆየው የ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ማዕቀፍ መሆኑን አይ ኤም ኤፍ ገልጿል።

በአልቫሮ ፒሪስ የተመራ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የባለሙያዎች ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከሕዳር 3 እስከ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቆይታ አድርጓል።

ቡድኑ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋሙ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ አማካኝነት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፕሮግራም እያደረገ ያለው ድጋፍ አፈጻጸምና የኢትዮጵያ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስመልክቶ ውይይት አድርጓል።

አልቫሮ ፒሪስ ቡድኑ በኢትዮጵያ የነበረውን ተልዕኮ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከገንዘብ ሚኒስትትር አሕመድ ሺዴ፣ ከገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ባንኮችና የንግድ ተቋማት ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በገበያ ወደ ሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ስርዓት ያደረገችው ሽግግርን ጨምሮ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በውጭ ምንዛሪ ግብይት ስርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ በመደበኛ እና የትይዩ ገበያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ከ10 በመቶ በታች እንዳወረደው የቡድኑ መሪ ገልጸዋል፡፡

የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ግምገማ በባለሙያዎች ደረጃ የተደረሰውን ስምምነት በቀጣይ ሳምንታት እንደሚገመግም ገልጸዋል።

የቦርዱ ግምገማ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ 251 ሚሊየን ዶላር ገደማ ገንዘብ እንደሚለቀቅም ጠቁመዋል።

ቀጣይ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ግምገማዎች በየስድስት ወሩ እንደሚካሄዱ ፒሪስ መግለጻቸውን የአይ ኤም ኤፍ የፕሬስ መግለጫ ያመለክታል።