Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በምሥራቅ ሐረርጌ የጦር አዛዥን ጨምሮ 7 ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በምሥራቅ ሐረርጌ የጦር አዛዥ ፉዓድ ሀሰን ኢብራሂምን ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች ከ3 እስከ 13 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹም 1ኛ በምሥራቅ ሐረርጌ የሸኔ የሽብር ቡድን አዛዥ ፉዓድ ሀሰን ኢብራሂም፣ 2ኛ የሸኔ የሽብር ቡድን ታጣቂ ቦንሳ ሀቂብ ሼክዳውድ፣ የመንግሥት ሠራተኛ የሆነው አብዱልወሃብ ሀሰን አህመድ፣ ነጃሃ መሀመድ እንድሪስ እንዲሁም ተማሪ የሆኑት ሙና አብዱልጀበል እንድሪስ እና ኡርጂ ሸምሰዲን አሊ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ በፌደራል ፖሊስና በሀገር መከላከያ ሰራዊት ጥምረት በክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(U) (ለ)፣ 35 እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 3(2) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 31(U) (1)፣(2)፣(3) የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ በየተሳትፎ ደረጃቸው በ2014 ዓ.ም ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በቀረበው ክስ እንደተጠቀሰው÷ ተከሳሹ ከሌሎች ያልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በዋና ወንጀል አድራጊነት በመላ አሳባቸውና አድራጎታቸው በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ በሙሉ ተካፋይ በመሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተፈረጀው የሸኔ አሸባሪ ቡድን ውስጥ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የሸኔ የምሥራቅ ሐረርጌ ሰራዊት አዛዥ ሆኖ በመስራትና በስሩ ከ28 በላይ የሸኔ ታጣቂ ወታደሮችን እየመራ ለሽብር ተግባር በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች የተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በ2013 ዓ.ም ሐምሌ ላይ የአሸባሪው ሸኔ አባል በመሆን ተመልምሎ ወደ ኬንያ በመሄድ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ በ2014 ዓ.ም ሕዳር ላይ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጭናክሰን ወረዳ ዳሪሙ ጋራ ላይ መሽጎ የነበረውን በ1ኛ ተከሳሽ የሚመራ የሸኔ ሽብር ቡድን የምሥራቅ ሐረርጌ ጦር መቀላቀሉ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ሕዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 6 ሠዓት ገደማ 1ኛ ተከሳሽ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቁ የሸኔ ወታደር ግብረ አበሮቹን እየመራ መደበኛ የህግ ማስከበር ስራቸውን ለማከናወን በቦታው ላይ በተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ሚሊሻ እንዲሁም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ምሥራቅ ዕዝ አባላት ላይ ተኩስ እንዲከፍቱ ትእዛዝ በመስጠትና ራሱም ክላሽንኮቭ መሳሪያ ታጥቆ በመተኮስ፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ተኩስ በመክፈት በቦታው የነበሩ ሁለት ግለሰቦችን በመግደል አንድ ግለሰብ ላይም የአካል ጉዳት በማድረስ የሽብር ተግባር ፈጽመው ከአካባቢው መሰወራቸው በክሱ ተጠቅሶ በፈፀሙት የሽብር ወንጀል ተከሰዋል፡፡

2ኛው ክስ ደግሞ በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን÷ በዚህም ተከሳሾቹ ከሌሎች ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ታኅሣስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 9 ሠዓት ገደማ በድሬዳዋ አስተዳደር ለገዶን ቀበሌ ገበሬ ማህበር በሚገኝ ተራራ ላይ 1ኛ ተከሳሽ የሽብር ቡድኑን ወታደሮች በመምራት፣ ትእዛዝ በመስጠትና ክላሽንኮቭ መሳሪያ ታጥቆ በመተኮስ፤ 2ኛ ተከሳሽ ወታደር ሆኖ ትእዛዝ በመቀበል 30 የክላሽንኮቭ ጥይትና ኤፍ 1 ቦንብ በመታጠቅ በወቅቱ መደበኛ የወንጀል መከላከል ስራ ለመስራት በቦታው ተገኝተው በነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ በመክፈት የሽብር ተግባር መፈጸማቸው ተጠቅሷል።

እንዲሁም 3ኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን÷ ይኸውም ተከሳሹ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 29(1) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ፤ በክሱ ላይ የተጠቀሱ አራት ተከሳሾችን ለሸኔ አባልነት በመመልመል እንዲያደራጁ፣ ለሽብር ቡድኑ ገንዘብ እንዲያሰባስቡ እና የጦር መሳሪያና ሎጅስቲክስ ማሰባሰብ ስራ እንዲሰሩ ተልእኮ በመስጠት ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረጉ በክሱ ተዘርዝሯል።

አብዱልወሃብ ሀሰን የተባለ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ የሽብር ወንጀል አፈፃፀምን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ እያመቻቸ ወይም እየረዳ መሆኑን እያወቀ በተመሳሳይ ቦታ መሽገው ከነበሩት የሸኔ ሽብር ቡድን አባላት ጋር በመገናኘት በተለይም ከቡድኑ መሪ 1ኛ ተከሳሽ ተልእኮ በመውሰድ በወረዳው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን እንቅስቃሴ እየተከታተለ በስልክ ለ1ኛ ተከሳሽና ላልተያዙት የሽብር ቡድኑ አባላት መረጃ ሲሰጥ እንደነበር በክስ ዝርዝሩ ተጠቅሷል፡፡

ሌሎች ተከሳሾች ደግሞ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 31(U) (1)፣(2)፣(3) የተመለከተውን መተላለፍ በተለያዩ መጠኖች ለሽብር ቡድኑ ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር በክስ ዝርዝሩ ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ በተከሳሾች ላይ ክሱ ከተመሰረተ እና የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦባቸዋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም፤ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል (ማስተባበል) አለመቻላቸው በፍርድ ቤቱ ተረጋግጦ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ አስተያየትን እና የተከሳሾቹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ የጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

እንዲሁም የመንግሥት ሰራተኛ የሆነውና መረጃ በማቀበል ወንጀል የተከሰሰው አብዱልወሃብ ሀሰን አህመድ በ3 ዓመት ከ 3 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም ነጃሃ መሀመድ እንድሪስ የተባለችው ተከሳሽ እና ተማሪ የሆኑት ሙና አብዱልጀበል እንድሪስ እንዲሁም ኡርጂ ሸምሰዲን አሊ የተባሉት ተከሳሾች እያንዳንዳቸውን በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version