አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪ ሕግን በተከተለ አግባብ ተግባራዊ እንዲደረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ውሳኔ አሳለፈ፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ በበይነ መረብ ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዚሁ መሠረትም በመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ፣ ለልማት ተነሺ ግለሰቦች ምትክ መሬት ማስተላለፍ፣ 19ኛው የብሔር ብሔረረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።
በመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ አፈጻጸም ሂደት ዙሪያ የመከረው ምክር ቤቱ÷ ካለፍው የጥቅምት ወር ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪ ህግን በተከተለ አግባብ ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የልማት ተነሺዎችን ምትክ ቦታ መስጠትን በተመለከተም÷ በከተማ መልሶ ማልማት ምክንያት ተነሺ የሆኑ ግለሰቦች ምትክ ቦታ ወይም የመንግስት ቤት አዘጋጅቶ መስጠት ተገቢ እና ህጋዊ መሆኑን በማመን የቀረበውን አጀንዳ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በ19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ላይም ባደረገው ውይይት÷ በዓሉ በታላቅ ድምቀት እንዲከበር የመስተዳድር ምክር ቤቱ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ በማሳሳብ እና የስራ አቅጣጫዎችን አሰቀምጧል፡፡