የሀገር ውስጥ ዜና

ብልፅግና ፓርቲ አግላይነትን በማስቀረት እኩልነት ማስፈኑ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

November 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ያለፈውን የአግላይነት ስርዓት አስቀርቶ አካታችነትንና እኩልነትን አስፍኗል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

“የሀሳብ ልዕልና፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ-ግብር በክልል ደረጃ ዛሬ በሠመራ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት÷ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ሰፍነው የቆዩትን የአግላይነት ስርዓትን በማስቀረት እኩልነትንና አካታችነትን በተግባር ያሳየና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው።

በብልፅግና ፓርቲ ክልሉ በመሳተፍ ፍትሃዊ የሆነ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን እያጠናከረ እና እያጎለበተ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ፓርቲው በጠንካራ አመራር በመመራት የጋራ የሆኑ ለውጦችን ማሳካት ችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፓርቲው በሂደት የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል ቁርጠኝነት ያለውና አመራር አባላቱም ይህንን ሚና እየተወጡ መምጣታቸውንም አስታውቀዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሁሴን በበከላቸው÷ ፓርቲው ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ስራዎች እንዲሰሩና ለውጦች እንዲመጡ አድርጎል ብለዋል።

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉ ወገኖች ወደ ሀገር እንዲገቡ እና በልማት እንዲሳተፉ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

ከክልል፣ ዞንና ወረዳ የተውጣጡ አመራር አባላት በተገኙበት የማጠቃለያ መርሐ-ግብሩ ተካሂዷል።