Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

5ኛው የብሪክስ ሸርፓስ ጉባዔ በሩሲያ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 5ኛው የብሪክስ ሸርፓስ (ሶስ-ሸርፓስ) ጉባዔ በሩሲያ ኢካተሪንበርግ ከተማ ተከፍቷል።

ጉባዔው በፈረንጆቹ 2024 በሩሲያ ሊቀመንበርነት የተደረገውን የመጨረሻውን ስብሰባ ለመገምገም ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

የሩሲያው ሼርፓ እና የጉባዔው ሊቀመንበር ሰርጌ ራብኮቭ ባደረጉት ንግግር÷ በፈረንጆቹ 2024 የብሪክስን ክንውኖች ማለትም የካዛን የመሪዎች ጉባዔ መግለጫና የ ”ብሪክስ ካንትሪ ፓርትነር ሞዴል”ን ጨምሮ ለብሪክስ መስፋፋት መንገድ መጥረጉን ተናግረዋል፡፡

ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአዳዲሶቹ አባል ሀገራት መካከል ያለው ውህደት እየተጠናከረ መምጣቱንም በአፅንዖት ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የልዩ ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ምኒልክ ዓለሙ ሩሲያ በፕሬዚዳንትነት ጊዜ ላሳየችው ጥሩ አመራርና በፈረንጆቹ 2024 የተቀላቀሉት የብሪክስ ሀገራትን ያለችግር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ያሳየችውን ቁርጠኝነትን አመስግነዋል።

በብሪክስ ሀገራት መካከልም በፖለቲካዊና ጸጥታ፣ በፋይናንስና ኢኮኖሚ፣ በህዝብ ለህዝብ ትስስር ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከር የኢትዮጵያን ቁርጠኝነት ማሳወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ጉባዔው ላይ በብሪክስ ቢዝነስ ካውንስልና በብሪክስ የሴቶች የንግድ አሊያንስ የተከናወኑ ተግባራትን ጨምሮ በኢኮኖሚና ፋይናንስ ጉዳዮች እንዲሁም በንግድ ለንግድ ግንኙነቶች ላይ በሊቀመንበሩ ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡

Exit mobile version