አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀጣናዊ ደህንነት ኦፕሬሽን ማዕከል (ሮክ) ዓመታዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ሮክ ስለ ስደትና ተያያዥ የወንጀል መረቦች መረጃን በተሻለ ለመከታተልና ለመለዋወጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተሻሻለ ክልላዊ አቅም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ እንዲሁም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት የጋራ ስልቶችን ማዘጋጀት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመዋጋት ጠንካራ አቋም እንድላትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና የሌሎች ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ኔትወርኮችን ለመበጣጠስ እና ለመከላከል ጠንካራ ቁርጠኝነት ያላት መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር በወንጀሉ የተጎዱትን በመጠበቅ ፣ የሚፈለጉ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር በማዋል በኩል በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በጉባዔው የሮክ ቴክኒካል ዳይሬክትር ሄርቪ ጃሜት፣ የሮክ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሙክታር ራማዴን እና የተለያዩ የሀገራት ተወካዮች መሳተፋቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡