Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተሀድሶ ስልጠና ያጠናቀቁ የሰላም ተመላሾች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ፓዊ ወረዳ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ 43 የሰላም ተመላሾች ተመረቁ፡፡

የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል መንገሻ ታከለ÷ የሰላም ተመላሾቹ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የትጥቅ ትግል ለማድረግ በመንቀሳቀስ በህብረተሰቡ ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡

የሰላም ተላሾቹ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ጥቅም የሌለው መሆኑን በመረዳት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መመለሳቸው ለሰላም መረጋገጥ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሰላም ተመላሾቹ መደበኛ የግብርና ስራዎችን ከመስራት ባለፈ መንግስት በሚያሰማራቸው በየትኛውም የግዳጅ ቀጠና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የጠላትን እኩይ ዓላማ ሊያከሽፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመተከል ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ደበሎ በበኩላቸው÷ የሰላም ተመላሾቹ የሰላም አስፈላጊነት በመረዳት ቀጠናው ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ ሰልጠኞች  የበደሉትን ማህበረሰብ መልሰው ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version