አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጣሊያን በታዳሽ ኢነርጂ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) የጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ጆርጅዮ ሲሊን ጋር መክረዋል፡፡
በውይይቱ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ የውሃ ሀብትን በማልማት፣ በመንከባከብና በመጠቀም ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ አብራርተዋል፡፡
በነፋስ ሀይልና ጂኦተርማልን ጨምሮ በታዳሽ ኢነርጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በተሻለ በርካታ ስራዎች እየሰራች እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተለይም በሶላር ላይ የሚሰራው ስራ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ግሪን ሀይድሮጅን ለማምረት ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመው፤ በኢነርጅም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
በኢነርጂና ውሃ ላይ ከሚሰሩት ስራዎች በተጨማሪ በመንገድ፣ በከተማ መሰረተ ልማት እና ከተሞችን የማስዋብና ለኑሮ ምቹ የማደረግ ስራ፣ በግብርናው ዘርፍም ስንዴን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስራ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ጆርጅዮ ሲሊን በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የሚሰሯቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ታዳሽ ሀይል ባለቤት መሆኗ በኢነርጂ ላይ ኢንቨስት ለማረግ አቅም እንዳለ፣ በቂ ውሃ ያላት ሀገር መሆኗም ግሪን ኢነርጂን በማምረት መጠቀም የምትችልበት ምቹ ሁኔታ እንዳለ እንዲሁም በፍጥነት እያደገች መሆኗን አንስተዋል፡፡
በዘርፉ የጣሊያን ተሞክሮ ምን እንደሆነም ገልፀው፤ በቀጣይም ሀገራቸው በታዳሽ ኢነርጂ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡