Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሕንድ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ትብብር እንደምታደርግ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕንድ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ማሻሻያ በብሪክስ ማዕቀፍ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር አኒል ኩማር ራኢ አረጋገጡ፡፡

ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የልማት ትብብርና ሌሎች ግንኙነቶችን ለማጠናከር ብሪክስ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ብሪክስ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ዕድገት ለማፋጠንና በዓለም አቀፍ መድረክ ያለውን አሰላለፍ በማስተካከል ሚዛን ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ሀገራቸው በብሪክስ አማካኝነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ብሪክስ ኢትዮጵያ ከሕንድና ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር ትብብርና አጋርነትን ለማጠናከር፣ ልምድና ዕውቀትን በመለዋወጥ ለመሥራት እንደሚያስችላት አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ ምጣኔ ሃብት በመገንባት ብልጽግናን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን ሪፎርም በብሪክስ ማዕቀፍ ለማገዝ ሕንድ ዝግጁ መሆኗንም ነው ያረጋገጡት፡፡

በልማት ሥራዎች የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት፣ በዕውቀትና ስትራቴጂ በትብብር በመሥራት ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ሕንድ ከኢትዮጵያ ጎን ትቆማለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትብብርን ለማጠናከር ጠቃሚ ያደርጋታል ነው ያሉት፡፡

 

Exit mobile version