Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከአየር መንገዱ ጋር ተያይዞ በወንጀል የተከሰሱት እነ ዮሃንስ ዳንኤል ላይ የምስክር ቃል መሰማት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ችሎት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተያይዞ በወንጀል የተከሰሱት እነ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃል መሰማት ተጀመረ።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ የተባሉት ስድስት ተከሳሾች ላይ የወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል

ተከሳሾቹ በነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3 ሰዓት ከ30 በሚሆንበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ መቐለ ከተማ ለመጓዝ አውሮፕላኑ ለበረራ ዝግጁ ቢሆንም በወቅቱ የነበረው የአየር ሁኔታ ለበረራ አዳጋች በመሆኑ በበረራ ባለሙያዎች በረራው ተሰርዞ እንዲወርዱ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ባለመሆን፣ ሌላውን መንገደኛም በማነሳሳት፤ አውሮፕላንን ያለአግባብ በመያዝ፣ የመንግስት ሰራተኛ የስራ ግዴታውን እንዳይፈጽም መቃወምና አለመታዘዝ ወንጀል ክስ እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ከሁለት ሰዓታት በላይ የተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ ቲክቶክ በተባለ ማህበራዊ ሚዲያ በቀጥታ የአየር መንገዱን መልካም ስም ለማጉደፍ በተንቀሳቃሽ ምስል ማሰራጨት ወንጀል የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህ መልኩ በክሱ ላይ በዝርዝር የቀረበባቸውን የወንጀል ተግባር አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ 15 ምስክሮች ቃል እንዲሰማለት በጠየቀው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ዛሬ የምስክሮቹን ጭብጥ በማስያዝ ምስክር ማሰማት ጀምሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version