አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አትሚስ) ቀጣይ የሃይል ስምሪት የቀጣናውን ደህንነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሆን እንደሚገባው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን አስገነዘቡ።
ስምሪቲ በጥንቃቄ ካልተመራ በምስራቅ አፍሪካ የደህንነት ስጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ምሁራኑ አስጠንቅቀዋል።
ምሁራኑ በፈረንጆቹ 2025 መጀመሪያ ላይ የሚደረገው የሀይል ስምሪት ወደ ተግባር ከመግባቱ አስቀድሞ የቀጣናውን ወቅታዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሊዋቅር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህር እና ተመራማሪ አብዱ መሀመድ አሊ (ዶ/ር)÷ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አወቃቀር ላይ ግዛቶች ጥያቄ የሚያነሱበት እንደሆነና በተገቢው መልኩ ያልተዋቀረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው አል-ሻባብ ከሀገሪቱ አልፎ በቀጣናው ቀውስ እንዳይፈጥር ለመከላከል አትሚስ የመከላከል ስራውን በብቃት ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በፈረንጆቹ 2025 አትሚስ ግዳጁን ጨርሶ ሲወጣ በቀጣይ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ሊያረጋገጥ በሚችል መልኩ መከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ይሁን እንጂ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት የድህረ አትሚስ ስምሪትን በተመለከተ የያዘው አቋም ቀጣናውን ከነበረበት መረጋጋት ወደከፋ ቀውስ የሚከት እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጫና ማሳደር እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።
የሶማሊያ መንግስት ጥያቄ የኢትዮጵያ ወታደሮች የከፈሉትን መሰዋዕትነት ያላከበረ ነው ያሉት አብዱ መሀመድ አሊ (ዶ/ር)÷ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት የኢትዮጵያን አስተዋጽኦ ዋጋ ለማሳጣት የሄደበት እርቀት የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት እና ምርምር ማዕከል የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ ሰራዊት በላይ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ዋጋ የከፈለ ሀይል የለም ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ የሞቃዲሾ መንግስት ይህንን ችላ ብሎ የቀጠናውን ሰላም ከማይፈልጉ ሀይሎቸ ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ቀጣዩ የአትሚስ የሀይል ስምሪት በጥንቃቄ የማይሰራ ከሆነ እንደ አል-ሻባብ እና አልቃኢዳ አይነት የሽብር ቡድኖች በቀጠናው እንደ ልብ እንዲንቀሳቀሱ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በፈረንጆቹ አዲስ አመት ተግባራዊ የሚደረገው የአትሚስ የሀይል ሰምሪት የቀጠናውን ሰላም በሚያረጋግት መልኩ ሊከናወን እደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ከዚህ በፊት እንዳስታወቀው፤ በሶማሊያ ከአትሚስ በኋላ የሚደረገው የኃይል ሥምሪት በቀጣናው ላይ አዲስ ውጥረት መፍጠር የለበትም፡፡
የሚከናወነው የኃይል ሥምሪት በቀጣናው ላይ አዲስ ውጥረት በመፍጠር በሰላም እና መረጋጋት ላይ አደጋ ሊፈጥር በማይችል መልኩ በጥንቃቄ ሊዋቀር እንደሚገባ ኢትዮጵያ እምነቷን መግለጿ ይታወሳል።
በሚኪያስ አየለ