አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ሃይል 89ኛ የምስረታ በዓል በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡
በዓሉን አስመልክቶ በቢሾፍቱ ከተማ የአፍሪካ አየር ሃይል ፎረም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በፎረሙ የአፍሪካ አየር ሃይል መሪዎችና በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት አታሼዎች እየተሳተፉ ሲሆን ፥ መድረኩ የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ትብብር መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ሃይል የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች የታጠቀ እና ብቁ የሰው ሃይል ያፈራ መሆኑ በፎረሙ ተነስቷል፡፡
ይህን ይበልጥ በማጠናከርም በ2022/23 ዓ.ም በአፍሪካ ተመራጭ አቪዬሽን ለመሆን እየሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ፎረሙ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፉ ያላትን የረጅም ዓመት ልምድ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለማካፈል እንዲሁም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እንደሚረዳ ተመላክቷል።
በተለያዩ መርሐ-ግብሮች አየተከበረ የሚገኘው 89ኛው የኢትዮጵያ አየር ሃይል የምስረታ በዓል በቀጣዩ ዓርብ ደግሞ የማጠቃለያ መርሐ-ግብሩ በቢሾፍቱ አየር ሃይል ሐረር ሜዳ ጊቢ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡
በታሪኩ ለገሰ