ቴክ

ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት መከሩ

By yeshambel Mihert

November 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካካል በሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት በተፈረመ ስምምነት መሰረት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለመጎብኘት፣ ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)÷ በዘርፉ ትልቅ ልምድ ካላት ደቡብ አፍሪካ የምርምርና ልማት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ኢኖቬሽንና ኢንዱስትሪያላይዜሽን፣የሰው ሃብት ልማት፣የምርምር ባለሙያዎች ትብበር እንዲሁም የጋራ መሰረተ ልማት ዝርጋታና አጠቃቀም ዙርያ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውጤታማነት የአፍሪካውያን ትብብር ማሳያዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትርብሌድ ንዚማንዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ደቡብ አፍሪካ በስፔስና አስትሮኖሚ፣ በምርምርና ኮመርሻላይዜሽን፣ በባዮ ኢኮኖሚ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በናኖቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ልማት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈልና የኢትዮጵያን ልምድም ለመቅስም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በናኖ ቴክኖሎጂ፣ በስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ በማቴሪያል ሳይንስ እንዲሁም በሰው ሃብት ልማት ትኩረት በመስጠት የአፍሪካን የ2063 አጀንዳ አፍሪካውያንን በማስተባበር እንዲሁም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ያላቸውን ትብብር በማጠናከር ሌሎችን የአፍሪካ ሀገራት መሳብና ማቀናጀት እንደሚጠበቅባቸው መገለጹንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በዘርፉ የጋራ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል የጋራ ፈንድ በማፈላለግና በመመደብ ለመስራትም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡