Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሻምፒየንስ ሊጉ ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያድርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የምድብ 5ኛ ዙር ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ቀጥለው ሲካሄዱ ሊቨርፑል እና ሪያል ማድሪድ አንፊልድ ላይ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ምሽት 2 ሠዓት ከ45 ላይ የሰርቢያው ሬድ ስታር ቤልግሬድ ከጀርመኑ ስቱትጋርት እንዲሁም የኦትስሪያው ስትሩም ግራዝ ከስፔኑ ዢሮና ይጫወታሉ፡፡
በሌላ የጨዋታ መርሐ-ግብር ምሽት 5 ሠዓት የመረሲሳይዱ ሊቨርፑል አንፊልድ ላይ የውድድሩ የ15 ጊዜ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያ የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡
ሊቨርፑል በመድረኩ እስካሁን ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፈ ሲሆን÷ በፕሪሚየር ሊጉ እያሳየ ያለው አስደናቂ አቋም እንዲሁም የሪያል ማድሪድ በሻምፒየንስ ሊግ ምሽቶች ያለው ወደር የለሽ ታሪክ ጨዋታው በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡
በሪያል ማድሪድ በኩል ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሺየስ ጁኒየር በጉዳት በጨዋታው የማይሰለፍ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሠዓት ላይ አስቶንቪላ ከጁቬንቱስ፣ ቦሎኛ ከሊል፣ ሴልቲክ ከክለብ ብሩጅ፣ ዳይናሞ ዛግሬብ ከቡሩሺያ ዶርቱመንድ፣ ሞናኮ ከቤኒፊካ እንዲሁም ፒኤስቪ ከሻካታር ዶኔስክ ይፋለማሉ፡፡
ትናንት ምሽት በተደረጉ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ያልተጠበቁ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን÷አርሰናል ስፖርቲንግ ሊዝበንን 5 ለ 1 ሲያሸነፍ ባየርን ሙኒክ ፒኤስጂን 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ፌይኑርድን 3 ለ 0 ሲመራ ቢቆይም ውጤቱን ማስጠበቅ ባለመቻሉ 3 ለ 3 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ኤሲ ሚላን ብራቲስላቫን 3 ለ 2፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ስፓርታ ፕራግን 6 ለ 0፣ ባርሴሎና ብረስትን 3 ለ 0፣ ባየርሊቨርኩሰን ሬድ ቡል ሳልዝበርግን 5 ለ 0፣ ኢንተር ሚላን አርቢ ሌብዢግን 1 ለ 0 እንዲሁም አትላንታ ያንግ ቦይስን 6 ለ 1 አሸንፈዋል፡፡
Exit mobile version