አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መድረሷ ተሰምቷል፡፡
በዚህም በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይዎት ለነጠቀው በእስራኤል እና በሊባኖስ ሂዝቦላ መካከል የተፈጠረው ግጭት እንዲያበቃ መንገዱ እየተደላደለ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ስምምነቱ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ስምምነት መደረጉ የተሰማው የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የሚመራው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመምከር የተጠራውን ስብሰባን ተከትሎ እንደሆነም ነው የተጠቆመው፡፡
ሆኖም በሊባኖስ የተካሄደው የእርቅ ስምምነት እስራኤል ከፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ ጋር እየተፋለመች ባለችውና ከፍተኛ እልቂት ባስተናገደችው ጋዛ የተኩስ አቁምና የታገቱትን የመልቀቅ ስምምነት ላይ የተባለ ነገር እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱ የእስራኤል ወታደሮች ከደቡብ ሊባኖስ ለቀው እንዲወጡ እና የሊባኖስ ጦር በአካባቢው እንዲሰማራ እንደሚያስገድድ ተሰምቷል፡፡
ሂዝቦላህ ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ ባለው ድንበር ላይ በትጥቅ እንዳይቆይ ይደረጋልም ነው የተባለው፡፡
የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላ ቡ ሀቢብ የእስራኤል ወታደሮች ሲወጡ የሊባኖስ ጦር ቢያንስ 5 ሺህ ወታደሮችን በደቡብ ሊባኖስ ለማሰማራት ዝግጁነት እንዳለውና በእስራኤል ጥቃቶች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ረገድ አሜሪካ የበኩሏን ሚና እንደምታደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
እስራኤል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሊባኖስ ጋር የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ውጤታማ እንዲያደርግ የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቃለች፡፡
በዚህም ሀገሪቱ ለሚደረግባት ማንኛውም ጥቃት ምንም ትዕግስት እንደማታሳይ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ካትስ ተናግረዋል ።
ይህ ስምምነት ከመደረሱ ሰዓታት በፊት እስራኤል የሂዝቦላህ ምሽግ ነው የተባለውን የቤሩትን ደቡባዊ ዳርቻዎች መምታቷን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡
በዚህም ቢያንስ ሠባት ሰዎች ሲሞቱ ፤ 37 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውም ነው የተነገረው፡፡
ሆኖም እስራኤል እስካሁን በሀገሪቱ ቡድኑ ይኖርበታል ያለችውን 20 ሥፍራዎች ንጹሃን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበርም ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሂዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬት መተኮሱንም ቀጥሏል ነው የተባለው እንደሬውተርስ ዘገባ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ባለስልጣን በሊባኖስ እየደረሰ ያለው የደም መፋሰስ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም ድርጅቱ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በእስራኤል የአየር ድብደባ ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ ፥ ከእነዚህም መካከል ሴቶች፣ ህጻናትና የህክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል ብሏል።
ባለፈው ዓመት በሊባኖስ ከ3 ሺህ 750 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ፥ ከ1 ሚሊየን በላይ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ሲል የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ አሳውቋል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን እስራኤል እና በጎላን ኮረብታ ሂዝቦላህ ባደረገው ጥቃት 45 ንፁሀን ዜጎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ፥ በእነዚህ አካባቢዎችና በደቡብ ሊባኖስ በተደረገ ውጊያ ቢያንስ 73 የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።