አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ የዲጂታል መረጃ ፍሰትን ለመፍጠር የሚያስችል ድረ-ገጽ አስለምቶ ተረክቧል፡፡
ድረ-ገጹ መንግሥታዊ መረጃን በፍጥነት፣ በጊዜ ተገቢነትና ኀላፊነት በተሞላበት መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም አሁን ያለውን የዲጂታል ዓለም የመረጃ ፍጥነት ያገናዘበ የመንግሥት የመረጃ ፍሰትን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ድረ-ገጹ ዓላማ ተኮር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አቅጣጫዎችን የሚከተሉ፣ መንግሥትና ሕዝብን የሚያቀራርቡ፣ የሕዝቡን ፍላጎት ለመንግሥት የሚያሳዩ፣ የመንግሥትንም ፍላጎትና ተነሣሺነት ወደ ሕዝቡ የሚያወርዱ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መሠረተ ልማቶችን አስተሳስሮ የያዘ የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት ነው ተብሏል፡፡
ድረ-ገጹ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃንን እና የማንኛውም መረጃ ፈላጊ ፍላጎት ለማርካት የመንግሥትን ዕቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ተግባራትን የተመለከቱ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የሚያስችል ነው።
እንዲሁም ከአገልግሎቱ መረጃዎች ባሻገር የፌዴራል ተቋማትንና የክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማትን መረጃዎች ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበት ሥርዓትንም ማካተቱን የኮሙኒኬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ያለማው ድረ-ገጹ ዜጎች በተለያዩ የመንግሥት እና የክልል የቋማት ላይ ያላቸውን ጥያቄ፣ አስተያየት እና ቅሬታ የሚያቀርቡበትንም አሠራር የያዘ መሆኑ ታውቋል፡፡