አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ኬንያ በወታደራዊ መስክ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይውይይት ተካሂዷል፡፡
በኬንያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሐሪሪ የተመራ ወታደራዊ ልዑክ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና ከኃይልና ከዋና መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ ተወያይቷል።
በዚሁ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረውን የሀገራቱን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በወታደራዊ ትብብር መስክ አብረን ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምተናል ብለዋል።
ሀገራቱ አልሸባብን በጋራ ከመከላከል ጀምሮ በፀጥታና ደህንነት በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጅት ተጠናቋል ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
ጄኔራል ቻርለስ ካሐሪሪ ኢትዮጵያና ኬንያ ለቀጣናው ደህንነት ወሳኝ ሀገሮች መሆናቸውን በመግለጽ÷ ወታደራዊ ግንኙነቱን ይበልጥ በማጠናከር ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል።
የአየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳና የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ይመር መኮንንም÷ ለልዑኩ የሰራዊት ዝግጁነት የስልጠና ተቋማትና ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ያላትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።